Why+was+the+MLC+adopted+Seafarers+need+special+protection

ለመርከብ ስራ ና ለባህረኞች ቅርብ የሆንን ረዘም ላለ ግዜ የምናቀው እውነታ አለ። የኢትዮጵያ ወጣት ባህረኞች ለረጅም ግዜ ብሶታቸውን የህግ ያለህ እያሉ ለመንግስትም ሆነ በደሉንም እያደረሰ ላለው ድርጅት ሲያቀርቡ ነበር። በአንድ በኩል በመንግስት ስልጣን ተሰጥቷቸው ነገር ግን አያገባኝም በሚል የሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች፡ ሲላቸው በማስፈራራት፡ ሲላቸው ደግሞ በቀጠሮ በማመላለስ ቅረታ አቅራቢ ባህረኞቹን ሲያንገላቱ ነበር። በደል አድራቹ ድርጅትም በቀደመው መንግስት የተሰጠውን በጥቅም የታሰረ መብት ከለላ አድርጎ ባህረኞቹን ቦታ ሰጥቶም አላነጋገረም። ከቀናት በፊት ፋና ራድዮ የነዚህን ተበዳይ ባህረኞችን አድምጦ ባደረገው ዘገባ በመጠኑም ቢሆን ያለውን እውነታ ለማሳየት ሞክሯል። ስለ ባህረኞቹ በደል እና ታያያዥ ጉዳዮች ከማንሳቴ በፊት መመለስ ያለበት ጥያቄ አለ። የኢትዮጵያ ባህረኞች በየትኛው የመንግስት መስሪያ ቤት ከለላ ስር ናቸው? ቅሬታ እና በደል ሲደርስባቸው ለማን ነው አቤት የሚሉት?

            እዚህ ላይ ባህረኞች ስንል በኢትዮጵያ መርከቦች ላይ የሚሰሩትን አይመለከትም። ምከንያቱም የኢትዮጵያ መርከቦች  በመንግስት ከለላ ስር ስለሆኑ እና ባህረኞቹም የራሳቸው የመተዳደርያ ደንብ ስላላቸው ችግራቸውን በሰለጠነ መንገድ ይፈታሉ። እዚህ ላይ ባህረኛ ብለን በአጠቃላይ የምናነሳው በግላቸው መርከብ ላይ ተቀጥረው የሚሰሩትን እና በ EMTI በኩል ሰልጥነው መርከብ ላይ የሚቀጠሩትን ነው።

በፋና ራዲዮ ላይ እንደሰማነው፡ በሚያስፍር ሁኔታ የትኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ሃላፊነት ወስዶ የባህረኛው ጉዳይ የራሴ ነው ሲል አልሰማንም። እውነት እንዳሉት የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን (EMAA) አይመለከታቸውም? MARITIME SECTOR ADMINISTRATION PROCLAMATION NO.549/2007 ከሚዘረዝረው አላማዎች መካከል አንዱ “በሃገሪቱ የዳበረና ቀጣይነት ያለው የማሪታይም ዘርፍ ክህሎት እንዲኖር ማድረግ” ነው ይላል። ክህሎት መፍጠር የሚቻለው ደግሞ የተመቻቸ የአሰራር ሁኔታ ሲኖር ነው። ሃገሪቷን ወደ ተሻለ ማሪታይም ኢኮኖሚ መፍጠር የሚቻለው መጀመሪያ የባህረኛው መብት ሲከበር ነው። ከዚሀ በተጨማሪም EMAA ስልጥና ውጭ አይመለከተኝም የሚል ከሆነ በአለም አቀፉ ስምምነት (Maritime Labour Convention – MLC) በተመለከተ National Contact Point ተብሎ የሚታወቀው የትኛው የመንግስት አካል ነው? ምንም እንኳን መላው አለም ያደነቀውን እና የባህረኞችን የስራ ሁኔታ የቀየረውን Maritime Labour Convention – MLC 2006 ኢትዮጵያ እስከ አሁን ባትፈርምም (ትንሿ ሃገር ጅቡቲ እንኳን ምንም ባህረኛ ሳይኖራት  በ 20 Jul 2018 ፈርማለች) ፡ ይህ ማለት ለመላው ባህረኛ የተሰጠው አለም አቀፍ መብት ለኢትዮጵያን ባህረኞች ተግባራዊ አይሆንም ማለት አይደለም። አሁንም ሆነ ወደፊት የባህረኛውን መብት ማስከበር ግዴታ ያለበት የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን (EMAA) ነው። በህንድም ሆነ በፊሊፒንስ ይህንኑ ሃላፊነት ወስዶ የባህረኛውን መብት የሚያስከብረው ከባህር እና መርከቦች ጋር ተያያዥነት ስራ የሚሰራው ማሪታይም ባለስልጣን ነው።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮችም (MOLSA) በአጠቃላይ የሰራተኛን የቅጥር ሁኔታ በተመለከተ የሚከታተል እንደመሆኑ መጠን በቀጣሪ እና በተቀጣሪ መካከል የሚከሰቱትን ችግሮች መርምሮ መስመር የማስያዝ ግዴታ አለበት። በተለይ በአሁን ሰአት አረብ ሃገር ተቅጥረው ለሚሰሩ ሰዎች በህግ እየተሰጣቸው ያለው ከለላ የሚያስደንቅ በሆነበት ሰአት፡ በሀገ-ወጥ መንገድ ባህረኞችን ወደ ውጭ እየላከ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ግን ወደ ራሱ ጀርመን አካውንት የሚያስቀረው ድርጅት EMTI/ EMA ግን ከ8 አመት በላይ ችላ ተብሎ ተቀምጧል።  ቢያንስ በቀጣሪ እና በተቀጣሪ መካክል ላለው ህገወጥ አስራር የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳዮች ሃላፊነት ወስዶ እርምጃ ሊወስድ ይገባ ነበር። ሲጀመር እንዴት ሆኖ ነው ሃገር ውስጥ ያልተመዘገበ እና ፈቃድ ያልተሰጠው ድርጅት መሃል ከተማ ትራኮን ህንጻ ላይ ቢሮ ከፍቶ ባህረኞችን ወደውጭ እየላከ ለ8 አመት ዝም የሚባለው? ባህረኞቹስ በስራ ምክንያት ውጭ ሲሄዱ ለሚደርስባቸው ችግር ዋስትና የሚሰጥው ማነው?

የባህር ላይ ስራ ሁለት መልክ ነው ያለው። በአንድ በኩል አስቸጋሪ እና አደገኛ ስራ ነው። ባህረኛው ህይወቱን እና ደህንነቱን አደጋ ላይ አድርጎ ነው ስራውን የሚሰራው።  ስለዚህም የመንግስትን ጥበቃ ይፈልጋል። በስራ ላይ ለሚደርስ ችግር በቀጥታ የሚመለከተው አካል በመንግስት በኩል በግልጽ መቅመጥ አለበት። ባህረኛውም ያለስጋት ሰርቶ መግባት መቻል አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ ባህረኛ ጥሩ ከሚከፈላቸው የስራ አይነት አንዱ ነው። የወር ደሞዝ ከተራ ባህረኛ 500 ዶላር ከሚከፈለው፡ እስከ 15000 ዶላር የሚከፈላቸው አንጋፋ ባህረኞች አሉን። መንግስት ባህረኛውን የመንከባከብ እና ለሌሎች አርአያ በማድረግ የሃገሪቷን የገቢ ምንጭ ማሳደግ አለበት። እንደ ህንድ እና ፊሊፒንስ ይህን ስለተረዱ ነው ባህረኞቻቸውን የተለያየ ድጋፍ በማድረግ የሚንከባከቧችው። መሰራታዊ መብታቸውን ከማስከበር አልፎም፡ በሃገራቸው በዶላር አካውንት እንዲከፍቱ መፍቀድ፡ ከቅረጥ ነጻ እድል ድረስ ድጋፍ መስጠት እና የትምህርት ማሻሻያ እድል የሚያመቻቹላቸው።

ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ስለ EMTI ትንሽ ልበል። የኢዮጵያ ማሪታይም ማሰልጠኛ ኢንስቲቱት EMTI የግል ድርጅት ሲሆን፤ ከ 8 አመት በፊት ከመንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ፈቃድ ተሰጥቶት ባህረኛ እያሰለጥነ ወደ ውጭ ገበያ ያቀርባል። የተመሰረተበት አላማ እና ከዛ በኋላ ያመጣቸው ለውጦች የተቀደሱ ቢሆንም፤ ወደኋላ ግን ባገኘው የመንግስት ክፍተት በመጠቀም፤ ወደ አላስፋላጊ ጥቅም እና የራሱን ስም ወደማጉደፍ ስራ ገባ። አሁንም በግሌ የማምነው ዋናው ባለቤቶቹ አላማቸው የተቀደሰ ነው፤ ሊበረታቱም ይገባል። ችግሩ ያለው ለማማከር እና የ እለት ተእለት ስራ እንዲያስተገብሩ የቀጠሯቸው እና አዲስ አበባ / ባህር ዳር ያስቅመጧቸው ሰዎች ናቸው። አንድም የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር፤ በሌላም የረጅም ግዜ እቅድ ከማውጣት ይልቅ ችግሮችን በማድበስበስ ሲላቸውም ባህረኛውም በማስፈራራት የአጭር ግዜ ብልጽግና እቅዳቸው አረጉ። በመንግስትም በኩል ከዚህ ቀደም ብሎ ክትትል ማድረግ ሲገባው፤ የባለስልጣን ዘመድ እስካሰለጠኑ ድረስ፤ ነገሮች እየተድበሰበሱ እስከ አሁን ለዚህ ደረሱ። የዚህ ጽሁፍ አላማም EMTI ያደረገውን ጥሩ ነገር ለማዋደቅ ወይም ወደፊት እንዳይቀጥል አይደለም። የዚህ ጽሁፍ አላማ EMTI እና ወጣት ባህረኞቹ መግባባት ላይ የሚደርሱበትን መስመር መጠቆም ነው። ለዚህ ደግሞ እስከ አሁን የተሰሩትን ብልሹ አሰራሮች ማንሳት ያስፈልጋል።

 ወደ ዋናው ጉዳይ ስንገባ፡ ስለ በአሁን ሰአት ወጣት ባህረኞቹ እያቀረቡ ያለው ቅረታ ምንድነው? መፍትሄ እና አስታራቂ አካሄዱስ እንዴት ነው? እነዚህን እና ተያያዥ ጉዳዮች እንመልከት።

 1. ከተቋሙ ሰልጥነው በተለያዩ ምክንያቶች ለረጅም ጊዜ ስራ ላይ ያልተሰማሩ ባህርተኞች –

EMTI ያሰለጠናቸውን ባህረኞች የተወሰኑት ወድያው ስራ ሲያገኙ፤ የተቅሩት ግን ምንም ግልጽ ባልሆነ አሰራር ቤታቸው ሆነው እንዲጥብቁ ይደርጋል። እድሉን አግኝተው መርከብ ላይ ሰርተው የተመለሱትም መቼ ወደ ስራ እንደሚመለሱ እንኳን ሳይታወቅ ትንሽ ያገኟትም ደሞዝ ብትሆን ተቆርጦ ነው የሚሰጥቸው። የሚቅጥለው ስራ እስከሚገኝ ድረስ ማንም አያስታውሳቸውም። ደሞዝ ለመቁረጥ እንደሚፈጥነው ሁሉ ቢያንስ የልጆቹን ሞራል ለመጠበቅ አግባብነት ባለው መንገድ ድጋፍ ማድረግ ይገባ ነበር። ለአንዳንድ ወጣት ባሀረኞች ከመርከብ የመኮብል ዋናው መንሰኤ ይህ ለረጅም ጊዜ ያለአስታዋሽ መቀመጣቸው ነው። ከባህረኞቹ ጋር በመመካከር መፍትሄ መፈለጉ አማራጭ ነው።

 1. ባህርተኞች ከ EMTI ጋር የገቧቸው የውል የስምምነቶች ያሉባቸውን ክፍተቶች –
  • ባህርተኞች ማንኛውንም አይነት እዳ ክፍያ ሲፈጽሙ ደረሰኝ አለመስጠት –
  • ባህረኞቹ ለስልጠና የተበደሩት እስከ 34000 ዶላር የሚደርስ እዳ በምን ሂሳብ እንደተሰላ ግልጽ አለመሆን –
  • ጁንየር ኦፊሰር እስከሚሆኑ የተያዘ 3000 ዶላር አለመመለስ –
  • አብዛኛዎቹ ውሎች ወደ አንድ ወገን ያጋደሉ ስለመሆናቸው –
  • የ ስልጠና እና ፓስፖርት የመሳሰሉ ዶኩመንቶች አስገድዶ EMTI ተይዘው እንዲቆዩ ስለማድረግ –
  • ባህርተኛው የመርከብ ስራ የሚያገኘው በ EMTI በኩል ብቻ ነው የሚለው –
  • የማሰልጥኛ እዳ ክፍያው በጥቅሉ ከመግለጹ ውጭ ምንም በዝርዝር ለምን እንደሚከፈል አለመገለጹ –
  • ለብድር ወይም ወደ ስራ ሲኬድ ተያዥ የሚጠየቀው –
  • ውሎች በሚሻሻልበት ግዜ ባህረኛው አለመማከሩ –

እንደ አንድ ትልቅ አላማ ይዞ ለተነሳ ድርጅት፤ እነዚህ ከላይ የተነሱት ቅረታዎች ባልተከሰቱ ነበር። ድርጅቱ የመረጥው ባህረኛን አሰልጥኖ ለውጭ ገበያ ማቅረብ በአጭር ግዜ ትርፍ የሚያስገኝ ቢዝነስ አይደለም። አንድን የድሃ ተማሪ ለ 6 – 8 ወር አሰልጥኖ 34ሺህ ዶላር ብድር ማስታቅፍ ዘረፋ ነው። ስልጥናው የሚሰጥው ባህርዳር ባዘጋጀው ካምፓስ ነው፤ ሁሉንም የትምህርት ወጭ የሚችለው ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ነው። EMTI የሚያወጣው ለአስተማሪዎች የሚከፍለው ደሞዝ ብቻ ነው። እሱንም የማስተማር አቅሙም ልምዱም ያላችው ሃበሾች እያሉ፤ ለራሱ ለ EMTI ብቻ ግልጽ በሆነ መንገድ አስተማሪ ከህንድ አስመጥቶ ነው የሚያስተምረው።

እንደ ስራ አስቀጣሪ ደግሞ ስናየው በ እናት ድርጅቱ EMA ስር ባህረኛውን ሲያስቀጥር የገቢ ምንጩ ከቀጣሪ መርከብ ድርጅት የሚያገኘው የወር ኮምሽን ነው። ከባህረኛው ላይ ምንም አይነት ክፍያም ጥቅምም ማግኘት የለበትም። ይህ አለም አቅፍ አሰራር እና በህግ የሚያስጥይቅም ነው። ነገር ግን እኛ ሃገር ይህን ጉዳይ እስከ አሁን የሚከታተለው ስለሌለ ባህረኛው የሚከፈለውን ደሞዝ እንኳን በቅጡ ሳያቅ ወደ ስራ እንዲሄድ ይደረጋል።

የስራ ውል በተመለከተም፤ አለም አቀፍ የባሀረኛ ደንቦች ከሚዘረዝሩት በተቅራኒ የ EMTI የስራ ውል የራሱን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ የተደረጉ ናችው። ባህረኛው ስራው ስለሚያጓጓውም፤ ጥያቄ ካቀረበም ስለሚባረር የተሰጥውን ውል ፈርሞ ወደ ስራ ይሄዳል። እግዚያብሄር እየጥበቃቸው ነው እንጅ በአደጋ ሆነ በ ችግር ግዜ ባህረኛው መብቱን ማስጠበቅ አይችልም።

ከላይ የተገለጹት ችግሮች ጥቅለል ባለ መልኩ ሊፈቱ የሚችሉት ባህረኞቹ ለራሳቸው እሚደራጁበት መንገድ በማመቻቸት እና የባህረኛ ማህበር በማቋቋም ብቻ ነው። የ ህንዶችን ስናይ በጣም የተደራጀ እና መንግስት ላይ ሳይቅር ተጽአኖ መፍጠር የሚችሉ የባህረኛ ማህበራት አሏችው። እነዚህ ማህበራት የባረኛውን መብት ለማስከበር የማይጓዙት እርቀት የለም። በተጨማሪም እነዚህ ማህበራት ባህረኛውን፤ መርከብ ስራ ቀጣሪው እና መንግስትን ያሳተፈ Tripartite Collective Bargaining Agreement (CBA) በመቅረጽ የሁሉንም መብት እና ግዴታ ያገናዘበ መተዳደርያ ስምምነት ያቅርባሉ። ይሀም አሰራራቸው ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ሁላችንም የምናቅው ነው። እኛም ከነሱ ልምድ ወስደን ሶስቱ የሚመለከታቸው አካላት፡ ባህረኛው ቀጣሪውና መንግስት ለኛ ሃገር ባህረኞች የሚመጥን መተዳደርያ ደንብ – Collective Bargaining Agreement (CBA) መቀረጽ አለበት። ለዛ ደግሞ ባህረኛው ሃሳቡን በአንድነት የሚያስተጋባበት የራሱ ማህበር ያስፈልገዋል።

 1. የ‘EMTI S.C’ ወደ ስልጠና ለሚያስገባቸው ባህርተኞች የሚደረግ የብቁነት ህክምና ምርመራ –

ከሌሎች ሃገራት ልምድ እንደምናየው የባህረኛ የብቁነት ህክምና ምርመራ በሚመለከተው የመንግስት አካል ስር ነው የሚሆነው። በእኛ ሃገር የዚህ ሃላፊነት የተሰጠው ለማሪታይም ጉዳዮች ባለስለጣን ነው። ባለስልጣኑም እውቅና ሰጥቶ የብቁነት ህክምና ምርመራ እንዲሰጡ የፈቅደላቸው ሁለት ሃኪሞች ብቻ ናችው። አንደኛው አዲስ አበባ የሚገኘው ሲሆን ሌላኛው ባህር ዳር ነው።

የብቁነት ህክምና ምርመራ በተመለከተ ግልጽ በሆነ የጥቅም ግጭት (conflict of interest) EMTI እጁን ነው ማውጣት ያለበት። ከስልጠናም በፊት ሆነ በኋላ የሚደረግ ምርመራ EMTI በራሱ ማድረግ አይችልም። ይህን በብችኝነት መክታተል ያለበት እውቅና በሰጣቸው ሃኪሞች አማካኝነት ማሪታይም ጉዳዮች ባለስለጣን ነው። በተለይ ካቀረቧቸው ቅረታ አንዱ፤ በ 8 ወር ውስጥ ከስልጠና በፊት የአይን ምርመራ ያለፈ ልጅ፤ ከስለጠና በኋላ ሊወድቅ አይችልም። ምክንያቱም የአይን ምርመራ ለ 5 አመት ስለሚያገለግል። በ8 ወር ውስጥ እይታ ሊቀየርም አይችልም። በዚህ ሁኔታ የተባረሩ ልጆች ካሉ እንደገና መታየት አለበት።

 1. አንድ ባህርተኛ የተመደበበት እና እፈልገዋለሁ ብሎ የያዘው የመርከብ ድርጅት ለረዥም ጊዜ ቢያቆየው ሌላ ድርጅት እንዲፈለግለት እና አንድ ድርጅት ባህርተኛውን ያለስራ የሚያስቀምጥበት ጊዜ የተገደበ እንዲሆን

ባህረኛው ሲሰራ ነው ደሞዝ የሚከፈለው። አንድ ድርጅት አንድን ባህረኛ እፈለገዋለሁ ካለ፡ መልሶ የሚወስድበትን ግዜ መወሰን አለበት። ከዚያ በላይ ሳይወስድ ካስቀመጠው በየወሩ የተወሰነ መክፈል አለበት። ይህ የቅንነት መጉደል ወይም የባህረኛውን መብት ከማራከስ አንጻር ካልሆነ በስተቀር መፍትሄው ግልጽ ነው።

ባህረኛውም ድርጅት የመቅየር ነጻነት አለው። አንድ ድርጅት ቶሎ መልሶ ካልወሰደው በራሱ ግዜ ሌላ ድርጅት እንዲቀጠር መመቻቸት አለበት። ከዚህ ጋር በተያያዘም፤ EMTI ግልጽነት በተሞላበት ሁኔታ የባህረኛው ምደባ ሁኔታ በተወሰነ የጊዜ ሰለዳ ማስታወቅ አለበት። ሌሎች የውጭ ድርጅቶች እንደሚያረጉት መቼ ባህረኛው ወደ መርከብ እንደሚመለስ ማሳወቅ አለበት። ይህ ሁሌም ባይሳካም ቢያንስ ባህረኛው እንዳልተረሳ ተስፋ እንዳይቆርጥ ያደርጋል።

 1. የ‘EMTI S.C’ አሰራር ግልጽና ተጠያቂነት ፡፡
  • ባህርተኞችን ወደ ስራ የሚመድብበት መስፈርት ምን መሰረት አድረጎ እንደሆነ ግልጽ አይደለም የትምህርት ውጤት ወይስ ሌላ ማወዳደሪያ ነጥብ እንዳለ ቢታወቅ፡፡
  • ቀድመው የተመረቁና ስራ የሚመደቡበት መንገድ እንዲመቻች ወይም ቀድመው ተመርቀው የሚጠብቁ ተቀምጠው አዳዲስ ተመራቂዎችን የሚመድብበት ሁኔታ ቢሰተካከል
  • በባህርተኞችና በ EMTI ቢሮ ላይ ያሉ ሰራተኞች መካከል ያሉ ግኑኝነቶች ቀናነት የተሞላበት ቢሆንና በህርተኞች ለሚገጥማቸው ችግሮች መፍትሄ ላማምጣት ሁሉም በቀናነት እና በመግባባት ችግሮችን ቢፈቱ

ከላይ እንደገለጽኩት ቢሮ ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች ቅንነት መጉደል፤ ከባሀረኛው ጥቅማጥቅም መፈለግ ካልሆነ እንጅ እነዚህን ቅሬታዎች በአግባቡ ማስተናገድ ከባድ ሆኖ አይደለም። ከሁሉም በላይ አዳዲስ ልጆች ሲቀጠሩ ወይም ለድርጅት ፕሮፖዝ ሲደረጉ ያለውን አሰራር ነጻ እና ግልጽ ማድረግ ነው። ምንም የሚደበቅ ነገር ስለሌለው። አንድ ድርጅት የተወሰኑ ባህረኞች እፈለጋለሁ ሲል፡ እነማን ለኢንተርቪው እንደተዘጋጁ፤ እነማን እንደተመረጡ፤ እነማን ደግሞ መጠባበቂያ መዝገብ ላይ እንዳሉ በግልጽ የሚታይበት አሰራር መዘርጋት አለበት። ባህረኛውም በፈለገው ሰአት EMTI ቢሮ ሄዶ ይህን መዝገብ ማየት መብት አለው። በተሻለም ይህን መረጃ በኢንተርኔት መጋራት ይቻላል።

 1. ባህርተኞች ከመርከብ የሚጠፉበትን ወይም የሚኮበልሉበት ሁኔታ-

ይህ ችግር EMTI በተደጋጋሚ ለስራዬ እንቅፋት ሆነብኝ ብሎ ሲያነሳ ይሰማል። በ EMTI ቢሮ በኩል የሚነሳው ዋናው ነጥብ ባህረኞች ከመርከብ ስለሚኮበልሉ ሌሎቹን ማስቀጠር አልቻልኩም ነው። ባህረኛው የሚለው ደግሞ እዚህ እንግልት ስለሚደርስብን እና ሰሚ ስለሌለን ነው የሚንኮበልለው ነው። የ እንቁላል እና ዶር የትኛው ይቀድማል አይነት ክርክር እስካለሆነ ድረስ ከሁለቱም አካል ውጭ ሆኖ ለሚመለከተው ሰው ግልጽ ይመስለኛል። በግሌ የባህረኞቹን ምክንያት በከፊል እደግፋለሁ። አንደኛ ነገር ለ 6 – 8 ወር ስለጠና 34000 ዶላር እዳ የተጫነበት ልጅ፤ ከዛም ስራ ለመጀመር አመታት የሚተብቅ ከሆነ በሚቀጥለው እድሉን ሲያገኝ ከመርከብ ቢኮበልል አይደንቀኝም። ሁለተኛ ይህንን ችግር ለመቅረፍ EMTI የሚሄድበት መንገድ ህገወጥ ነው። በተለይ ደግሞ ይህንን ችግር ይቀርፋል ተብሎ አዲስ አበባ ቤሮ ሃላፊነት የተሰጠው ሰው ያራሱን ኑሮ ለማደላል ሲል እውነታዎችን እየደበቀ፤ ባህረኞቹን ድምጻቸው እንዳይሰማ በማድረግ ለአመታት እየተንከባለለ አሁን ለመቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ አድርሶታል።

እኛ ሃገር ምናልባትም ለመጀመሪያ ግዜ በግል ድርጅት Polygraph (lie detector test) የሚሰጥ ድርጅት EMTI ብቻ ነው።  ወጣቶቹ ከራሳቸው ፈቃድ ውጭ ከማስገደድ ባልተናነሰ ሁኔታ ውጭ ሃገር ሄደው ይቀራሉ አይቀሩም ብሎ ለማወቅ Polygraph (lie detector test) እንዲወስዱ ይደረጋሉ። ይህን ለማድረግ አንድ ሰው ከ እስራኤል ይመጣል። ጎበዝ ይህ ህጋዊ ነው??? ወንጀል የሰራ ሰው እራሱ Polygraph (lie detector test) ለማድረግ የራሱ የህግ አሰራር አለው። እንዴት ሆኖ ነው አንድ የማሰልጠኛ ድርጅት ሰራተኛን በ Polygraph (lie detector test) የሚፈትሽው? ከዛስ በኋላ በአሰሪው እና ሰራተኛው መካከል ጤናማ ግንኙነት ይኖራል? በሚቀጥለውስ ማለፍ አለማለፌን በምን አቃለሁ? መሳርያውስ ምን ያህል ታማኝነት አለው? የሰው ህይወት እንዴት በ አንድ መሳርያ ውጤት ይወሰናል? ከዚህ በኋላስ ባህረኛው ቢኮበልል ይደንቃል?

አሁን በቅረቡ ደግሞ Polygraph (lie detector test) እንዳልሰራ ሲገባቸው የ አንድ ሚሊዮን ብር ደረቅ ቼክ አምጡ ብለዋል። በድጋሜ ይህ አሰራር ኢሰብአዊ ከመሆን በዘለለ ህገወጥም ነው። አንዳንዴ ቢሮ ቁጭ ብለው እንደዚህ አይነት አስቂኝ እና አስገራሚ የአጭር ግዜ መፍትሄ የሚያመጡት ሰዎች የአይምሮ ብቃታቸው ያሳስበኛል። ድርጅቱንም ወደ አላስፈላጊ ውድቀት እየወሰዱት ነው።

እንደኔ እምነት የባህረኞቹ የመኮብለል ችግር ከነዚሀ ያለፈ ነው። ዋና ምክንያቶቹ፤

 1. ከስልጠና በፊት የሚደረግ የማጥራት አሰራር ውጤት ተኮር አለመሆን
 2. የሚሰለጥነው ባህረኛ እና ስራ አግኝቶ የሚቀጠረው አለመመጣጠን
 3. በስልጠና ግዜ የሃበሻውን ባህል እና አስተሳሰብ የሚረዳ ሃበሻ ሳይሆን ህንዶች ስለሚያሰለጥኗቸው
 4. በስልጠና ግዜ በቂ ክትትል አለመኖር
 5. በ EMTI እና በ ባህረኛው መካከል መተማመን ስለሌለ
 6. ባህርተኞችን ያለሙያቸው መመደብ – ኢንጅነሪንግ የተመረቀን ሰው ተራ ዝቅ ያለ ስራ አስቀጥሮ መላክ
 7. የስለጠናው ወጭ የሃገሪቷን የኑሮ ሁኔታ ያገናዘበ አለመሆን
 8. EMTI ባህረኛውን የሚመለከትበት መንገድ ትክክል ስላልሆነ – ባህረኛው ሲኖር ነው EMTI የሚኖረው
 9. በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚደረግ የተሳሳተ የቢዝነስ ስትራቴጂ

ከላይ የተገለጹት ምክንያቶች ጊዜ ተወስዶ በጥናት የተደገፈ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ናቸው።  በተጨማሪም ሁሌ የኮበለሉትን ብቻ ከማስታወስ፤ ሳይኮበልሉ ተሳክቶላቸው ትልቅ ቦታ የደርሱትን ባህረኞች እንደ ሮል ሞድል በማሳየት እና የጀማሪ ባህረኞችን ሞራል በመገንባት ከዚህ አዙሪት ችግር መውጣት ይቻላል።

 1. ከቅጥር ጋር በተያያዘ፡
  • ባህርተኞች ከመርከብ ላይ በስራ ወቅት ለሚድርስባቸው ማንኛውም አይነት አካላዊ ጉዳት ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙና አጠቃላይ ባህርተኞች መርከብ ላይ በሚያሰልፈው ወቅት የህይወታቸው ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የ‘EMTI S.C’ የሚኖረውን ሃላፊነት ከባህርተኞው ተያዥ ጋር ሌላ ስምምነት እንዲወስድልን እና የ‘EMTI S.C’ ድርሻ ተለይቶ እንዲታወቅ
  • አንድ ባህርተኛ ወደ ስራ ትሄዳለህ ተብሎ በረራ ትኬትና ሌሎች መረጃዎች ከተሟላለት በኋላ ጉዞው ሲሰረዝ ለባህርተኛው ያወጣዉን ወጭ እንዲከፈለው፡፡ ይህ ማለት አንድ ከክፈለ አገር ያለ ባህርተኛ በፍጥነት ደረስ ነገ ወይም በዚህ ሳምንት ወደ ስራ ትሄዳለህ ከተባለና የስራ ውል ፈርሞ የበረራ ትኬት ወስዶ ሁሉን ከጨረሰ በኋላ በተለያየ ምክንያት ጉዞው ለተወስነ ጊዜ ተራዝሟል ይባላል ይህ ግን ባህርተኛውን ለአላስፈላጊ ውጭ ስለሚዳርገው መፍትሄ ቢበጅለት
  • በተለያዩ ምክንያቶች አንድ ባህርተኛ ከመርከቡ ሳይደርስ ከመንገድ ቢመለስ ችግሩን የፈጠረዉ አካል ተጠያቂ የሚሆንበትንና ባህርተኛውም ላጠፋው ወጭ ክፍያ እንዲያገኝና ችግሩ መፍትሄ ሳያገኝ ስራው ከተቋረጠ ተገቢውን ክፍያ እንዲያገኝ ይደረግ ለዚህም ምሳሌ ለማቅረብ አንድ ባህርተኛ ወደ ስራ መረከቧን ለማግኘት የተለያዩ ጉዞዎችነ ያደርጋል ሆኖም በመሃል የአንድ አገር ቪዛ ሳይዝ ወይም በሌላ ምክንያት ከብዙ እንግልት በኋላ እንዲመለስ ይደረግና ባህርተኛው ላልታወቀ ጊዜ ስራ አጥ ይሆናል ይህ የሆነው ግን የ‘EMTI S.C’ ሰራተኛ በፈጠርው ስተት ነው ስለሆነም እንዲሰተካከል ቢደረግ

ይህም ቅድም ካነሳሁት የ መተዳደርያ ደንብ ጋር ተያያዥነት አለው። ባህረኛው ተደራጅቶ የራሱ መተዳደርያ ደንብ ሲኖረው ይህ ችግርም አብሮ ይቀረፋል።

 1. ባህርተኞችን ያለሙያቸው መመደብ እንዲቆም በተለይ ኤሌክትሪካል ኦፊሰር ለመሆን ስልጥነው የኦይለር ሙያ ፍቃድ እንዲያወጡ የሚደረገው እንዲቀር

የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን (EMAA) ከስልጠና እና ሰርተፍኬት ውጭ እኔን አይመለከትም ብሎ ነበር። በዚህ እና በተመሳሳይ የስልጠና እና ሰርተፍኬት ችግሮችን ግልጽ አቋም የለውም። ደረጃ የጠበቀ ባህረኛ የማፍራት አላማው እስካለን ድረስ፤ EMTI የአቀደውን እና እየተገበር ያለውን መከታተል የ EMAA ሃላፊነት ነው። አንድ ባህረኛ በሰለጠነበት የስራ መስክ ነው መስራትም ያለበት። ኦይለር እና ዋይፐር ለማሰልጠን ከፈለገ በ ዲግሪ የተመረቁ መካኒካል እና ኤሌክትሪካል ኢንጅነሮች አይደሉም ለቦታው የሚመጥኑት። በ ዲግሪ የተመረቁ መካኒካል እና ኤሌክትሪካል ኢንጅነሮችን ወስደን ኦይለር እና ዋይፐር የምናሰራ ከሆን ምናልባትም በ አለም ላይ እራሳችንንም ሃገራችንንም መሳለቂያ እያረግን ነው።

 1. ለአገራችን የዉጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ባህርተኞች ውለታቸው ለአገር ታላቅ ስለሆነ በመንግስት እውቅና እንዲያገኙና ተገቢውን ጥቅማጥቅም የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች

ይህ ጥያቄ ምንም እንኳን ከ EMTI ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ባይሆንም፤ ባህረኞቹን ትስስር ለማጠንከር የተለያዩ አበረታች ነገሮች ማረግ ይችላል። ለምሳሌ አሁን የደረሰበትን ሁኔታ ባላቅም በ አንድ ወቅት ለ ባህረኛው የቤት እና መኪና መግዣ የብድር አገልግሎት ከተወሰኑ ባንኮች ጋር ሲያመቻች ነበር። ይህ እና መሰል አበረታች ነገሮች ባህረኛውን ተስፋ እንዲኖረው እና ለ EMTI ያለውን አመለካከት የሚቀይር ነው። በተጨማሪም እንደ አመታዊ የ እራት ግብዣ፤ የውይይት መድረክ፤ ስለጠና የመሳሰሉትን ነገሮች አዘጋጅቶ ባህረኛው እንዲገናኝ እና ልምድ እንዲለዋወጥ ቢደረግ አሁን የተነሱት ችግሮች አብዛኛው ባልተከሰቱ ነበር።

 1. የ‘EMTI S.C’ እና የ‘EMA’ ግኑኝነታቸውና አሰራራቸው እንዴት ነው ምክንያቱም ውል የምንዋዋለው ከ‘EMTI S.C’ ሲሆን ስራ የሚያገኝልን ደግሞ የ‘EMA’ ስለሆነ ስራ ባለማግኝታችን የምንጠይቀውን አካል ለይተን ለማወቅ ስለተቸገርን ይህንን ጥያቄ ልናነሳ ተገደናል፡፡ ስለሆነም የ‘EMA’ አላማ ና ተግባሩ ምንድን ነው?

መጀመሪያ ‘EMTI S.C’ እና የ‘EMA’ ግልጽ እናድርግ። ‘EMTI S.C’ በአቶ መለስ ዜናዊ ዘመን እውቅና ተሰጥቶት ባህረኛን እንዲያሰለጥን ህጋዊ ፈቃድ ያለው የውጭ የግል ድርጅት ነው።  ስልጠናውም የሚሰጠው በ ባህር ዳር ሲሆን የሚሰጠውም ስልጠና በ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ እውቅና አለው። በርግጥም ለማስተማር የሚያፈልጉት ቁሳቁስ ጨምሮ፤ የመማርያ ህንጻ፤ የተማሪ መኖርያ፤ የተማሪ ምግብ፤ ዩኒፎርም የሚያሟላው ይህው ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ነው። በወቅቱ ከ ባሀር ዳር ዩኒቨርስቲ ጋር Memorandum Of Understanding ሲፈራረሙ ግልጽነት በጎደለው መንገድ EMTI S.C ከ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ጋር ተጣብቆ ሲሰራ በ አንጻሩ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ምን ጥቅም እንደሚያገኝ እንኳን አልተገለጸም። 34000 ዶላር አንድን ባህረኛ የሚያስከፍለውም ምን ያህሉ ለ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ይድረሰው የሚታወቅ ነገር የለም። ምናልባትም ምንም አይደርሰውም፤ ምክንያቱም ስምምነቱ የተፈረመው በ አቶ መለስ ጊዜ ስለነበር።

ወደ EMA ስንመለስ፤ EMA ዋና መስርያ ቤቱን በ ጀርመን ሃገር ያደረገ የኢትዮጵያ ማሪታይም አጀንሲ የሚባል ነው። EMA በ አጭሩ የሰለጥኑትን ባህረኞች ስራ የሚያስቀትር ነው። ቅርንጫፍ ቢሮው ትራኮን ህንጻ ላይ ነው። በ ሰራተኛ ና ማህበራዊ ባለስልጣን እውቅና የሌለው EMA ለ አለፉት 8 አመታት ባህረኞቻችንን ወደ ውጭ እየወሰደ ስራ ያስቀጥራል። ለምን በኢትዮጵያ ተመዝግቦ ፈቃድ አላወጣም? መልሱ ቀላል ነው። EMA እሰከ አሁን ሲያረገው የነበርው ነገር ሁሉ ወንጀል ስለሆነ እና ሲነቃበት ጠቅሎ ለመውጣት እንዲመቸው ነው። ይህ አሰራሩ ባለፉት አመታት ጥያቄ አላስነሱም፤ ምክንያቱም በሙስና የተዘፈቁት ባለስልጣኖቻችን፤ ሆዳቸው እስከሞላ ድረስ እና አንድ ሁለት ዘምዶቻቸው ስራ እሰከተቀጠሩ ድረስ ባላየ ያልፉት ነበር።

ከላይ እንደተገለጸው አንዱ ያሰለጥናል፤ ለላኛው ያስቀጥራል። አንዱ ህጋዊ ነው፤ ለላኛው ህገወጥ ነው። ሁለቱም እኛው ሃገር ነው ያሉት። ሁለቱም ባለቤታቸው አንድ ሰው ነው። ይህ አሰራር የተፈጠረውም ባህረኛውን ከማደናገር ባለፈ የ ሃላፊነት ብዥታ ለመፍጠር ነው። ከላይ EMTI ብቻ የተጠቀምኩትም ሁለቱ የ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ስለሆኑ ነው።

ወደ ባህረኞቹ ችግር ስንመለስ፡ እስከ አሁን ድረስ ወደ ውጭ ስራ እያሰቀጠረ የሚወስዳቸው ድርጅት በእትዮጵያ ውስጥ ህጋዊ ቦታ የለውም። ባህረኛው ችግር ቢደርስበት በህግ የሚጠይቀው አካል ሃገር ውስጥ የለም። በህግ የሚጠየቀው አካል ደግሞ ጀርመን ሃገር ነው ያለው። አንድ ደሃ ባህረኛ ጀርመን ሄዶ ሊከስ ነው? ይህንን መንግስት ነው ማስተካከል ያለበት።

በቅድሚያ EMA እንደማንኛውም ሰው ቀጣሪ አጀንሲ ሃገር ውስጥ በ ህጋዊ መንገድ መመዝግብ አለበት። ከተመዘገበም በኋላ በአለም አቀፉ ስምምነት (Maritime Labour Convention – MLC) መሰርት የ ባህረኛውን መብት እንዴት ማክበር እንዳለበት ለመንግስት ማሳወቅ አለበት። ይህ አለም አቀፍ ስምምነት (Maritime Labour Convention – MLC) ከ90 በላይ ሃገራት የፈረሙት እና በ አሁን ሰአት ባህረኛውን መብቱን አስከብረው የሚኖሩበት አሰራር ነው። እንደ ሃገር እና ILO Convention በ 1923 እንደፈረመች ግንባር ቅደም ሃገር እስከ አሁን Maritime Labour Convention መፈርም እና ህግችን ማድረግ ነበረብን። እትዮጵያ አለመፈረሟ ግን ባህረኞቻችን ከዚህ ተጠቃሚ አይሆኑም ማለት አይደለም። አሁን ባህረኞቻችን የዚህ አለም አቅፍ መብት ተጥቃሚ መሆን አለባቸው።

            ላማጠቃለል ያክል፤ ወጣት ባህረኞቻችን እያነሱት ያለው የ ፍትህ ጥያቄ ህጋዊ እና ወቅታዊ ነው። ችግሮቹን በችላታ ማልፍ የሃገሪቷን ኢኮኖሚ ከመጉዳትም በዘለለ ወደፊት የሰለጠኑ ባህረኞችን እስከ ማጣት ያድርሳል። በ አሁን ሰአት መፍትሄ የሚሆነው የተነሱትን ቅሬታዎች ሁሉንም ወገን ባከተተ መንገድ ቁጭ ብሎ በምክክር እና በ እቅድ ለመፍታት መሞከር ነው። በምንግስትም ስልጣን የተሰጠው አካል አያገባኝምን ትቶ ቢያንስ የማደራደሩን እና ወደ ጋራ ስምምነት የሚወስደውን መፍትሄ ለማቅረብ ቢሰራ ጥሩ ነው። EMTI S.C’ እና የ‘EMA’ ባህረኛውን ማዳመጥ ቢጀመሩ ጥሩ ነው። ከላይ የቀረቡት የመፍትሄ ሃሳቦች ቢተገበሩ ወደፊት በይበልጥ ተጠቃሚ የሚሆነው EMTI S.C’ እና የ‘EMA ነው።

            ሃሳብዎን በ comment ላይ ይላኩልኝ። ወይም በ ኢሜይል capt.yigezu@yahoo.com ይላኩ። አዳዲስ ሃሳቦችን ና ሂሶችን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።

4 thoughts on “የወጣት ኢትዮጵያን ባህረኞች የፍትህ ጥያቄ

 1. Good job, well explained! The essue should go further. It neads a solution and responsible office should handle it. As a free country, It is shame this happened for years and yet no one willing to Step forward and tried to stop the crime behind it.
  This is slavery and Ema has no respect for Ethiopians. 34600$ for 6 months training😰.

  Like

 2. ካፕቴን ይገዙ እጅግ በጣም እናመሰግናለን ችግሮችን ለይተህ በጥልቅ ስለፃፍክልን የemti ትልቁ ችግር የ 34000$ እዳውና በአገራችን ema ፈቃድ አግኝቶ መስራት ናቸው እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን እየለየህ ለመፃፍ እንደሞከርክም አይተናል:: እኔ እምለው ይሄ 34000$ ሌላ ሀገር በስንት ነው የሚማሩት google አድርጌ ያየሁት በህንድ እስከ 4000$ እንደሆነ ሰምቻለው ታድያ እኛ የጥጃ ላም ነን እንዴ ዝም ብለን የምንታለበው?? i hope you sir will create an association for ethiopian seafarers and i’m on your side , thanks for your writing.

  Like

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s